Exodus 29

የካህናት መቀደስ

29፥1-37 ተጓ ምብ – ዘሌ 8፥1-36 1“ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉኝ ትቀድሳቸው ዘንድ የምታደርገው ይህ ነው፤ ነውር የሌለባቸው አንድ ወይፈንና ሁለት አውራ በጎች ውሰድ። 2እርሾ ከሌለው ከምርጥ የስንዴ ዱቄት ቂጣ፣ በዘይት የተለወሰ የቂጣ ዕንጐቻና በዘይት የተቀባ ኅብስት ጋግር። 3በሌማት ላይ አድርገህ ከወይፈኑና ከሁለቱ አውራ በጎች ጋር አቅርባቸው። 4ከዚያም አሮንና ወንድ ልጆቹን ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በማምጣት በውሃ ዕጠባቸው። 5ልብሶቹን ወስደህ ለአሮን አልብሰው፤ ሸሚዝ፣ የኤፉድ ቀሚስ፣ ኤፉዱንና የደረት ኪሱን አልብሰው፤ ኤፉዱን በእርሱ ላይ በጥበብ በተሠራ መታጠቂያ እሰረው። 6መጠምጠሚያውን በራሱ ላይ በማድረግ የተቀደሰውን አክሊል ከመጠምጠሚያው ጋር አያይዘው። 7ቅብዐ ዘይት ወስደህ በራሱ ላይ በማፍሰስ ቅባው። 8ወንዶች ልጆቹን አምጥተህ ሸሚዞች አልብሳቸው። 9የራስ ማሰሪያዎችንም አድርግላቸው
ዕብራይስጡ፣ የሰላም መሥዋዕት አድርግላቸው ይላል።
፤ ከዚያም አሮንንና ወንዶች ልጆቹን መታጠቂያዎችን አስታጥቃቸው፤ ክህነት የዘላለም ሥርዐት ይሆንላቸዋል፤ በዚህም መንገድ አሮንንና ወንዶች ልጆቹን ትክናቸዋለህ።

10“ወይፈኑን በመገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት በማምጣት አሮንና ወንዶች ልጆቹ በራሱ ላይ እጆቻቸውን ይጫኑበት። 11በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ዕረደው። 12ከወይፈኑ ደም ወስደህ በመሠዊያው ቀንዶች ላይ በጣቶችህ አድርግበት፤ የቀረውንም ከመሠዊያው ሥር አፍስሰው። 13ከዚያም በሆድ ዕቃዎች ያለውን ስብ ሁሉ፣ የጕበቱን መሸፈኛና ሁለቱንም ኵላሊቶች በዙሪያቸው ካለው ስብ ጋር ወስደህ በመሠዊያው ላይ አቃጥላቸው። 14ነገር ግን የወይፈኑን ሥጋ፣ ቈዳውንና የማይበላውን አሰስ ገሠስ ሥጋ ከሰፈር ውጭ አቃጥለው፤ የኀጢአት መሥዋዕት ነው።

15“ከሁለቱ አውራ በጎች አንዱን ወስደህ፣ አሮንና ወንዶች ልጆቹ በራሱ ላይ እጃቸውን ይጭኑበታል። 16አውራውንም በግ ዕረደው፤ ደሙንም ወስደህ በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን እርጨው። 17አውራ በጉን በየብልቱ ቈራርጠህ፣ የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን ዐጥበህ ከራሱና ከሌሎቹ ቍርጥራጭ ብልቶች ጋር አኑረው። 18ከዚያም አውራ በጉን በሙሉ በመሠዊያው ላይ አቃጥለው፤ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚቃጠል መሥዋዕት ጣፋጭ መዐዛና ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት ነው።

19“ሌላውን አውራ በግ ወስደህ አሮንና ወንዶች ልጆቹ በራሱ ላይ እጆቻቸውን ይጭኑበታል። 20አውራውንም በግ ዕረደው፤ ከደሙም ወስደህ የአሮንንና የወንዶች ልጆቹን የቀኝ ጆሮዎቻቸውን ጫፍ የቀኝ እጆቻቸውን አውራ ጣቶች፣ የቀኝ እግራቸውንም አውራ ጣቶች ቅባቸው፤ ከዚያም ደሙን በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን እርጨው። 21በመሠዊያው ላይ ካለው ደምና ከቅብዐ ዘይቱ ወስደህ በአሮንና በልብሶቹ ላይ እንዲሁም በወንዶች ልጆቹና በልብሶቻቸው ላይ እርጨው። ከዚያም እርሱና ወንዶች ልጆቹ እንዲሁም ልብሶቻቸው የተቀደሱ ይሆናሉ።

22“ከዚህ አውራ በግ ስቡን፣ ላቱን፣ በሆድ ዕቃው ውስጥ ያለውን ስብ፣ የጕበቱን ሽፋን፣ ሁለቱን ኵላሊቶችና በዙሪያቸው ያለውን ስብና ቀኙን ወርች ውሰድ፤ ይህ የክህነት አውራ በግ ነው። 23በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት በሌማት ካለው ያለ እርሾ ከተጋገረው ቂጣ፣ ዳቦ፣ በዘይት የተሠራ ዕንጐቻና ኅብስት ውሰድ። 24እነዚህን ሁሉ በአሮንና በወንዶች ልጆቹ እጆች ላይ በማኖር እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ወዝውዛቸው። 25ከዚያም ከእጃቸው ወስደህ ከሚቃጠለው መሥዋዕት ጋር ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መልካም መዐዛ እንዲሆን በመሠዊያው ላይ አቃጥለው፤ ይህም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት ነው። 26ለአሮን ክህነት የአውራ በጉን ፍርምባ ከወሰድህ በኋላ እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ወዝውዘው፤ ይህም የአንተ ድርሻ ይሆናል።

27“ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ ለክህነት የሆኑትን የአውራውን በግ ብልቶች ቀድሳቸው። የተወዘወዘውን ፍርምባና የቀረበውን ወርች 28ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ የዘወትር የእስራኤላውያን ድርሻ የሚሆነው ይህ ነው፤ ከኅብረት መሥዋዕታቸው
በትውፊት፣ የሰላም መሥዋዕት በመባል ይታወቃል።
እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚያቀርቡት ነው።

29“የአሮን የተቀደሱ ልብሶች ለትውልዶቹ ይሆናሉ፤ ይኸውም በእነርሱ ይቀቡና ክህነትን ይቀበሉ ዘንድ ነው። 30ካህን በመሆን እርሱን የሚተካውና በመቅደሱ ለማገልገል ወደ መገናኛው ድንኳን የሚመጣው ወንድ ልጅ ሰባት ቀን ይለብሳቸዋል።

31“የክህነቱን አውራ በግ ወስደህ ሥጋውን በተቀደሰ ስፍራ ቀቅለው። 32አሮንና ወንዶች ልጆቹ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ የአውራውን በግ ሥጋና በሌማት ያለውን ዳቦ ይብሉ። 33ለክህነታቸውና ለመቀደሳቸው ማስተስረያ የሆኑትን እነዚህን መሥዋዕቶች ይብሉ፤ የተቀደሱ ስለሆኑ ሌላ ማንም አይብላቸው። 34ከክህነቱ የአውራ በግ ሥጋ ወይም ከቂጣው እስከ ንጋት ድረስ ቢተርፍ አቃጥለው፤ የተቀደሰ ስለሆነ መበላት የለበትም።

35“ክህነታቸውን በሰባት ቀን በመፈጸም ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ ያዘዝሁህን ሁሉ አድርግላቸው። 36ለማስተስረያ የሚሆን አንድ ወይፈን የኀጢአት መሥዋዕት አድርገህ በየዕለቱ ሠዋ፤ ለመሠዊያውም ማስተስረያ በማቅረብ መሠዊያውን አንጻው፤ ትቀድሰውም ዘንድ ቅባው። 37ለሰባት ቀን ለመሠዊያው ማስተስረያ በማድረግ ቀድሰው፤ ከዚያም መሠዊያው እጅግ የተቀደሰ ይሆናል፤ የሚነካውም ሁሉ የተቀደሰ ይሆናል።

38“በየዕለቱ ያለ ማቋረጥ በመሠዊያው ላይ የምታቀርበው ይህ ነው፤ ዓመት የሞላቸው ሁለት የበግ ጠቦቶች፤ 39አንዱን በማለዳ፣ ሌላውን በምሽት አቅርብ። 40ከመጀመሪያው የበግ ጠቦት ጋር የኢፍ መስፈሪያ አንድ ዐሥረኛ
ይህ ምናልባት 2 ሊትር ያህል ነው።
ምርጥ ዱቄትን ተወቅጦ ከተጠለለ ሩብ ኢፍ
ይህ ምናልባት 1 ሊትር ያህል ነው።
ዘይት ጋር ለውስና ሩብ ኢን ወይንን ደግሞ የመጠጥ መሥዋዕት በማድረግ አቅርብ።
41ሌላውን የበግ ጠቦት በማለዳው እንደ ቀረበው ተመሳሳይ ከሆነው የእህልና የመጠጥ መሥዋዕት ጋር በምሽት ሠዋው፤ ይህም ጣፋጭ መዐዛና ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት ነው።

42“ይህ የሚቃጠል መሥዋዕት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ በሚመጡት ትውልዶች ዘወትር ይደረጋል፤ በዚያ እገናኝሃለሁ፤ እናገርሃለሁም፤ 43በዚያ ደግሞ ከእስራኤላውያን ጋር እገናኛለሁ፤ ስፍራውም በክብሬ ይቀደሳል።

44“ስለዚህ የመገናኛው ድንኳንና መሠዊያውን እኔ እቀድሳለሁ፤ ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉኝ አሮንና ወንድ ልጆቹን እቀድሳለሁ። 45ከዚያም በእስራኤላውያን መካከል እኖራለሁ፤ አምላካቸውም (ኤሎሂም) እሆናለሁ። 46በመካከላቸውም እኖር ዘንድ ከግብፅ ያወጣኋቸው እኔ አምላካቸው እግዚአብሔር (ያህዌ) መሆኔን ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) አምላካቸው ነኝ።

Copyright information for AmhNASV